Saturday, 16 February 2013

የባሮክ ደብዳቤዎች - በባሮክ መጽሃፈ (Letters from Abroad, Barok Metsihafe,Yemisirach Special Issue, August 2009 )

የውጭ ሀገር ምዕራፍ 
 የባሮክ ደብዳቤዎች (ባሮክ መጽፈ)
 
  • የምሥራች   /Yemisirach Special Issue, August 2009/
 እነዚህ ደብዳቤዎች ባሮክ አገር ቤት ላሉት አባቱ የጻፋቸው ናቸው። ባሮክ  እዚህ አገር እግሩ ከረገጠ ጀምሮ ላለፉት አራት ዓመታት ደብዳቤዎቹ አልተቋረጡም። በደብዳቤዎቹ የተገለጡት ገጠመኞች የግድ የባሮክ ገጠመኞች ብቻ ላይሆኑ ይችላሉ። እርሱ ለአባቱ ሲጽፋቸው የተሰማውንና የሚከነክነውን ጉዳይ ከማውጋቱና የጸሎትም ሆነ የመረዳት ድጋፉን ለአባቱና  አገር ቤት ላሉት ቤተሰቦቹ ከማጋራቱ  ውጪ ሌላ ፍላጎት ወይም ሃሳብ ኖሮት አይደለም።
 እነዚህ ገጠመኞች አብዛኛው በስደት የሚኖር ሰው ሊጋራው የሚችላቸው ይሆናሉ።  አንባቢዎቹም ባንድም ሆነ በሌላ መልኩ ራሳቸውን ሲያዩ ወይም ሲያገኙ የሚሰማቸው የተለያየ ስሜት ሊሆን እንደሚችል ጸሀፊው ይገነዘባል። ካስተዋልንና እውነቱ ካልጎመዘዘን፤ እግዚአብሔር በረዳን መጠን ያለንበትን በመረዳት ቆም ብለን እንድናመዛዝን፣ ራሳችንንም በማረቅ በህይወት መንገድ እንድንዘልቅ ያግዙናል ብሎ ያስባል። መልካም ንባብ።
 
እንደምነህ አብዬ?
እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። ሁሉንም ቤተሰብ እስቲ ሰላም በልልኝ። እምዬን ስትላት “ምነው ጸሎትሽ ዘገየ?” በላት።  ተሰቃየሁ እኮ አብዬ - የኔ ነገር ቁርጡ ሳይታወቅ መባነን ብቻ ሆኖ ቀረ እኮ? “ልንቀበልህ ነው” እያሉኝ አራት ዓመት ሆነኝ አይደል እንዴ? እስቲ በነገርና በምሬት አልጀምራችሁ ሁሉንም እርሱትና ጤናችሁን ብቻ ልስማው።
 
ስንት ጊዜ ሆነኝ ደብዳቤ ከላክሁኝ? አውቃለሁ ከሰሞኑ በስልክ ስለተገናኘን ናፍቆቴ በረድ ስላለ መሰለኝ። ሳስበው ግን አንድ ፊቱን ደብዳቤው ሳይሻል አይቀርም። ምክንያቱም እናንተም “ናፍቀትህ አስቸገረን” ለምትሉት ደጋግማችሁ ታነቡታላችሁ፤ እኔም ደርሶ እስኪመለስ ትንሽ ጊዜ አገኛለሁ። ደግሞስ ለጸሎት አጀንዳ ለመያዝ ሃሳቡን በዝርዝር ለማግኘት ይቀል የለ?
 
ዝርዝር አልኩ እንጂ ሳስበው ደግሞ “እሱስ ለምን  ያስፈልጋል?” እላለሁ። ቀኑ ከነጋ ጀምሮ እስኪመሽ ስጋትና “ምን ደብዳቤ ይመጣ ይሆን?” እያልኩ ቀልቤን ስቼ እየዋልኩ ለየትኛው ብለህ እንደምትጸልይና እንደምታጸልይ እዚህ ሆኜ እኔን ግራ ይገባኛል። ያ እሁድ ደርሶ ትንሽ ይገላግለኛል እንጂ የኔማ ጉዳይ ዘንድሮ የእንግሊዝን መንግስት ሳይሆን እኔኑ እያሳሰበኝ ነው።
 
“እሁድ እሁድ ምን አለ አልከኝ?” የቻልነውና ሽቀላ የሌለብን ቤተ ክርስቲያን እንደምንሰበሰብ ነግሬህ የለ እንዴ? እዚህ ሀገር እሁድ ለጸሎት ብቻ ሳይሆን ለገቢም ጥሩ ቀን በመሆኑ ሁሌም ‘የኔ’ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሞልተው አያውቁም። እነርሱም አይሞሉም፤ ፍላጎታቸው ሞልቶም አያውቅም፤ ወይም “በቃን” ሲሉ እኔም ሰምቼ አላውቅም። ደግሞ የብልጠታቸው ህሊናቸው እንኳን ቀርቶ  ሰው እንዳይወቅሳቸው እሁድ የሚሰራ ሰው ሽማግሌ አድርገው መምረጣቸው። የእግዜሩን ነገር ተወው፤ አሁን ህሊናም ቀርቶ እገሌ ሆኗል የበለጠ የሚፈራው። ምንም ይሁን ምን እሱው ይሻላል። በቃ ስድስቱን ቀናት ስባክን ቆይቼ፣ እንዳልኩህ ሲቻል አበሻ ከውስጡ ሳይሆን ጥርሱን ብቻ እየገለጠ ተሳስሞ ከሚለያይበት ከዚያው የመገናኛ ቦታችን እሁድ ስሳተፍ ቀለል ይለኛል።
 
 አብዬ፣ እዚህ ይኸውልህ ሰዉ የገባው ስለሆነ ነገር አያካብድም። ቅድም ስለ ቤተ ክርስቲያን ሳነሳብህ  ‘የኔ’ የምትለዋን በቅንፍ ያደረገኩት አውቄ ነው። “ደግሞ ከምኔው ቤተ ክርስቲያን ከፈትክ” እንደምትልና እንደምትጠረጥር ገብቶኛል። አይግረምህ አልከፈትኩም። አቅቶኝ ሳይሆን እግዜርን ፈርቼ ነው። ለመተዳደሪያማ ካልክ እሱ ሳይሻል እንደማይቀር ዛሬ ጊዜ ከፈሉት ‘ፓስተሮች’ መረዳት አያቅትህም። “የነጻነት ጉዶች” ብሎ በድፍረት የተናገራቸው ማን ነበር? አዎን ያን ዘማሪውን ደረጀ ከበደን “በሰው እንጀራ ለምን ይገባል?” እያሉ ሲያጉረመርሙ ስሰማ አልገረመኝም። ከምቾታቸውና ዓላማቸውን ከመሳታቸው የተነሳ እግዚአብሔርንም ቢያገኙት “አርፈህ ተቀመጥ!” የሚሉ እየመሰለኝ እኔ ለነርሱ ጨነቀኝ።
 
“ምን አገባህ” አልከኝ? እሱ አይደል እንዴ እዚህ አምጥቶ የሚያንከራትተኝ አብዬ? የማየውን ግፍና ከንቱነት በመቃወሜ ካገሬ መገፋቴ ሳያንሰኝ ቤተ ክርስቲያንም ውስጥ “ዓይናችሁን ጨፍኑ፣ እናሞኛችሁ” የሚሉ ብልጣ ብልጦች ከእግዜር ሲያጣሉን ሳይ ዝም ልበል? ተወኝ አብዬ! ይልቅ እስቲ እንጸልይ። የመጣብን ጣጣና ፍርጃ ሁሉ ከዚሁ ክፋትና ልቅነት የተነሳ እግዚአብሔር አዝኖብን ይመስለኛልና ዝም ብለን ብንጸልይ ሳይሻል እይቀርም። እውነት ነው፤ ሰሞኑን የተሰጠንን የነህምያን መጽሃፍ ዘጠነኛ ምዕራፍ ስናጠና ላለንበትና ለገጠመን ውርደትና ረሃብ ሁሉ መዘዙ የኛና የአባቶቻችን ከእግዚአብሔር ዓላማና መንገድ ፈቀቅ ማለት ሆኖ ነው የተሰማኝ። እባክህን እስቲ በያለንበት እንጸልይ።  ንስሃ ብንገባና ብንመለስ እኮ እግዚአብሔር ቀድሞ እንዳደረገው ምህረቱን ሊያበዛ ይችላል። እስቲ ፊቱ እንውደቅ አብዬ!

ውድ አባቴ፣ ዛሬ ልጽፍልህ ስጀምር የነበረው ሀሳቤ ምኑም ስላልተጨበጠልኝ ደብዳቤውን ላቋርጠው ነው። ብዙም ስለእንግሊዝ ሳልነግርህና ወሬዬም ሳይጣፍጥህ እንዳለቀ አላጣሁትም። አንዳንዴ እንደዛ ይሆናል። የቤተክርስቲያን ነገር ሲነሳ ያለ አቅሜ ቅናቱ አንበለበለኝ ልበል? ይሁን ግድ የለም ለበጎ ነው። በሚቀጥለው ግን ያ “ሆም ኦፊስ” ብዬ ባለፈው የነገርኩህ ሰውዬ የሰራኝን እጽፍልሃለሁ።

በቃ እንግዲህ ሰሞኑን ሰው ካገኘሁ፣ እንደሰዉ ያቺን በጥቁር ሰርቼ የተረፍኳትን መቶ ባውንድ እልክልሃለሁ። ያ ባለ ሱቁ አብዱራህማን ባሉት ጊዜ ማቀበሉ ልብ ቢያደርስም ከሷው ላይ ሲቀነጭብ ክፉኛ ስለሚጎዳት ግድ የለህም ሰው ሲመጣ ጠብቄ ብልክ ይሻላል። እስከዛው እናንተም ጸልዩ እዚህ እኔም እበረታለሁ።

 ልጃችሁ ባሮክ
እንግሊዝ።

Artist Seyoum Teffera

Interview with Artist Seyoum Teffera ("Yemedan Qen" Ministry)

http://www.youtube.com/watch?v=fFsdz1us6_Q&feature=share