የውጭ ሀገር ምዕራፍ
- የምሥራች /Yemisirach Special Issue, August 2009/
እንደምነህ አብዬ?
እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። ሁሉንም ቤተሰብ እስቲ ሰላም በልልኝ። እምዬን ስትላት “ምነው ጸሎትሽ
ዘገየ?” በላት። ተሰቃየሁ እኮ አብዬ - የኔ ነገር ቁርጡ
ሳይታወቅ መባነን ብቻ ሆኖ ቀረ እኮ? “ልንቀበልህ ነው” እያሉኝ አራት ዓመት ሆነኝ አይደል እንዴ? እስቲ በነገርና በምሬት
አልጀምራችሁ ሁሉንም እርሱትና ጤናችሁን ብቻ ልስማው።
ስንት ጊዜ ሆነኝ ደብዳቤ ከላክሁኝ? አውቃለሁ ከሰሞኑ በስልክ ስለተገናኘን ናፍቆቴ በረድ ስላለ መሰለኝ። ሳስበው
ግን አንድ ፊቱን ደብዳቤው ሳይሻል አይቀርም። ምክንያቱም እናንተም “ናፍቀትህ አስቸገረን” ለምትሉት ደጋግማችሁ ታነቡታላችሁ፤
እኔም ደርሶ እስኪመለስ ትንሽ ጊዜ አገኛለሁ። ደግሞስ ለጸሎት አጀንዳ ለመያዝ ሃሳቡን በዝርዝር ለማግኘት ይቀል የለ?
ዝርዝር አልኩ እንጂ ሳስበው ደግሞ “እሱስ ለምን
ያስፈልጋል?” እላለሁ። ቀኑ ከነጋ ጀምሮ እስኪመሽ ስጋትና “ምን ደብዳቤ ይመጣ ይሆን?” እያልኩ ቀልቤን ስቼ
እየዋልኩ ለየትኛው ብለህ እንደምትጸልይና እንደምታጸልይ እዚህ ሆኜ እኔን ግራ ይገባኛል። ያ እሁድ ደርሶ ትንሽ ይገላግለኛል
እንጂ የኔማ ጉዳይ ዘንድሮ የእንግሊዝን መንግስት ሳይሆን እኔኑ እያሳሰበኝ ነው።
“እሁድ እሁድ ምን አለ አልከኝ?” የቻልነውና ሽቀላ የሌለብን ቤተ ክርስቲያን እንደምንሰበሰብ ነግሬህ የለ እንዴ?
እዚህ ሀገር እሁድ ለጸሎት ብቻ ሳይሆን ለገቢም ጥሩ ቀን በመሆኑ ሁሌም ‘የኔ’ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሞልተው አያውቁም።
እነርሱም አይሞሉም፤ ፍላጎታቸው ሞልቶም አያውቅም፤ ወይም “በቃን” ሲሉ እኔም ሰምቼ አላውቅም። ደግሞ የብልጠታቸው ህሊናቸው
እንኳን ቀርቶ ሰው እንዳይወቅሳቸው እሁድ የሚሰራ ሰው ሽማግሌ
አድርገው መምረጣቸው። የእግዜሩን ነገር ተወው፤ አሁን ህሊናም ቀርቶ እገሌ ሆኗል የበለጠ የሚፈራው። ምንም ይሁን ምን እሱው
ይሻላል። በቃ ስድስቱን ቀናት ስባክን ቆይቼ፣ እንዳልኩህ ሲቻል አበሻ ከውስጡ ሳይሆን ጥርሱን ብቻ እየገለጠ ተሳስሞ
ከሚለያይበት ከዚያው የመገናኛ ቦታችን እሁድ ስሳተፍ ቀለል ይለኛል።
ውድ አባቴ፣ ዛሬ ልጽፍልህ ስጀምር የነበረው ሀሳቤ ምኑም ስላልተጨበጠልኝ ደብዳቤውን ላቋርጠው ነው። ብዙም
ስለእንግሊዝ ሳልነግርህና ወሬዬም ሳይጣፍጥህ እንዳለቀ አላጣሁትም። አንዳንዴ እንደዛ ይሆናል። የቤተክርስቲያን ነገር ሲነሳ ያለ
አቅሜ ቅናቱ አንበለበለኝ ልበል? ይሁን ግድ የለም ለበጎ ነው። በሚቀጥለው ግን ያ “ሆም ኦፊስ” ብዬ ባለፈው የነገርኩህ ሰውዬ
የሰራኝን እጽፍልሃለሁ።
በቃ እንግዲህ ሰሞኑን ሰው ካገኘሁ፣ እንደሰዉ ያቺን በጥቁር ሰርቼ የተረፍኳትን መቶ ባውንድ እልክልሃለሁ። ያ ባለ
ሱቁ አብዱራህማን ባሉት ጊዜ ማቀበሉ ልብ ቢያደርስም ከሷው ላይ ሲቀነጭብ ክፉኛ ስለሚጎዳት ግድ የለህም ሰው ሲመጣ ጠብቄ ብልክ
ይሻላል። እስከዛው እናንተም ጸልዩ እዚህ እኔም እበረታለሁ።
No comments:
Post a Comment